1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሥርዓት ለውጥ በቶጎ

ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 26 2016

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችም ሕገ-መንግስታዊ ለዉጡን ከመጠን በላይ በመንቀፍ ከዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰሮችና ከሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ጋር በመሆን ጉዳዩን ለዴሞክራሲያዊ መርሆዎች ቀጥተኛ ተግዳሮት እንደሆነ ሲገልጹት ቆይተዋል ።

https://p.dw.com/p/4fUK7
የቶጎ ፕሬዚዳንት ፋዉሬ ግናሲንግቤ
የቶጎ ፕሬዚዳንት ፋዉሬ ግናሲንግቤምስል Ute Grabowsky/photothek/IMAGO

የሚያዝያ 26 ቀን 2016 ትኩረት በአፍሪቃ

የሥርዓት ለውጥ በቶጎ
የቶጎ ፓርላማ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ አዲስ ሕገ መንግሥት በማፅደቅ በቶጎ ከፕሬዚዳንታዊ አገዛዝ ወደ ፓርላሜንታዊ ሥርዓት ለመሸጋገር የሚያስችለውን መንገድ ከፍቷል ።ይህ በሃገሪቱ ታላቅ አከራካሪ ነጥብ ሆኗል።  ይህም ከተቃዋሚ መሪም ሆነ ከሲቪል ማህበረሰቡ በፖለቲካው መስክ እየታየ ያለውን ለውጥ የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ፋዉሬ ግናሲንግቤ ሥልጣን ለማግበስበስ የሚያደርጉት ጥረት ነው በማለት ይተቻሉ።
ከፕሬዝዳንታዊ ሥርዓት ወደ ፓርላማዊ አገዛዝ መሸጋገሩ በቶጎ የፖለቲካ ሂደት አዲስ የፖለቲካ ባሕል እንደሆነ ይነገራል።
ሬነዋል የተባለው የተቃዋሚ ፓርቲ የድርጊት ኮሚቴ መሪ ዶድጂ ኤፔቮን ፤ ሕገ መንግሥቱን ለመቀየር የፓርላማው ውሳኔ መሻር አለበት ብለዋል ። "የሚያስከፍለን ዋጋ ምንም ይሁን ምን እንዋጋለን ፤ "ፕሬዝዳንት ግናሲንግቤ እያስገቡባቧት ካለው ጥልቅ ጉድጓድ አገራችንን ለማዳን በዚህ ምቹ ሁኔታ ዙሪያ ሁላችንም አንድ ነን" ብለዋል ። አክለውም

"ይህ ፖለቲካዊ ለውጥመላው የቶጎ ሕዝብ የቆመለትን ዓላማ ላይ  ሕገ መንግሥታዊ መፈንቅለ መንግሥት መፈጸም ነው"

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችም ሕገ-መንግስታዊ ለዉጡን ከመጠን በላይ በመንቀፍ ከዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰሮችና ከሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ጋር በመሆን ጉዳዩን ለዴሞክራሲያዊ መርሆዎች ቀጥተኛ ተግዳሮት እንደሆነ ሲገልጹት ቆይተዋል ።
የቶጎ የሰብዓዊ መብቶች ሊግ አባል የሆኑት ሴሌስቲን አግቦጋን ሕገመንግስቱን በመቀየር ወደ ፓርላሜንታዊ ሥርዓት ለመቀየር የሚደረገውን እንቅስቃሴ በአስቸኳይ እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል።
"የቶጎ ሕዝብ በዚህ አካሄድ ላይ ለዓመፅ ይነሳል ፤ የመንግሥት ኃላፊዎችም ይህንን ሕግ የማስወገድ ኃላፊነት አለባቸው ።"
የታብለማ ተቋም ፕሬዚዳንት ፖል አመጋክፖ ከአግቦጋን ጋር ይስማማሉ ፤ ለውጡን ለማቆም አለመቻል በአገሪቱ የፖለቲካ ቀውስ ሊያስከትል ይችላል ባይ ናቸው።
ግናሲንግቤ "የዕድሜ ልክ መሪ" ለመሆን እያሰቡ ነው።
ሕገ መንግሥቱን የመቀየር ውሳኔ በውጭ አገር በሚገኙ ቶጎአውያን ዘንድም ተቀባይነት አላገኘም።  በሰሜናዊው የጀርመን  ግዛት በሀምቡርግ ከተማ ውስጥ ለክርስትያን ዴሞክራቶች ፓርቲ ማለትም በምህጻሩ (ሲዲዩ) የአስተዳደር አማካሪና የክልል ፖለቲከኛ የሆኑት ክሌመንት ክሉትስ ከ20 ዓመት በፊት ከቶጎ ወደ ጀርመን አቅንተዋል።
የክሉትሴ አመለካከት በቶጎ ያሉትን ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሐሳብ ይጋራል። ለእሳቸውም ለውጦቹ የፕሬዚዳንቱን ሥልጣን ለማደለብናየዴሞክራሲያዊ እሴቶችን ለማዳከምየታሰቡ ናቸው ። በመሆኑም ግናሲንግቤ "የዕድሜ ልክ መሪ ይሆናሉ" ሲሉ ክሉትሴ ለDW ተናግረዋል ። 
"ሥልጣናትን ሁሉ በተለይም ኢኮኖሚያዊ ፣ ወታደራዊና ተቋማዊ ሥልጣኖችን በሙሉ ጠቅልለው  ይይዛሉ ።"

በሎሜ ከተማ የሚገኘው የቶጎ ምክርቤት ሕንጻ
በሎሜ ከተማ የሚገኘው የቶጎ ምክርቤት ሕንጻምስል Alphonse Logo/Anadolu/picture alliance


ይህ በቶጎ የታሰበው የሥርዓት ለውጥ ተቃዋሚዎችና በውጭ አገር የሚኖሩ የአገሪቷ ተወላጆች ቢቃወሙትም በአንጻሩ ተስፋ ያደረጉበትም አሉ። ሕብረት ለለውጥ የተባለ ድርጅት አባል የሆነችው አናቴ ኩመዓሎ ወደ ፓርላሜንታዊ ሥርዓት ስለሚደረገው ሽግግር ተስፋ እንደሚሰማት ገልጻለች። ይህም የሕገ መንግሥቱ ለውጥ በስፋት እየተደገፈ መሆኑን ያሳያል ባይ ናት ።

"አብዛኞቹ ቶጎዎች ይህን መንግሥት በጥብቅ የሚከተሉና አዲስ ልምድ ለመቅሰም ዝግጁ በመሆናቸው በሙሉ ድምፅ ተቀባይነት አግኝቷል ። ይህ በእርግጥም የእርካታና የኩራት ስሜት ነው ። "
አክላም "ይህ ሕገ መንግሥታዊ ለውጥ ብዙ ችግሮችን እንድንፈታ ፣ አገራችንን ዘላቂ ለሆነ ዕድገት እንድትበቃ ለማድረግ ያስችለናል" ብላለች ።
"ለእኛ ለቶጎ ህዝቦችን በተሻለ ሁኔታ ወደ አንድ ለማምጣት እንችል ዘንድ ከዚህ በፊት ያሰብነውን የሚመስል ሌላ ነገር መሞከር ይሻላል" ያሉት አሊፑይ አክለውም "ፍጹም የሆነ ነገር ስለሌለና አንድ ቦታ መጀመር ስላለብን ይህን ሕገ መንግሥት በተግባር ላይ ለማዋል እንጥራለን" ብለዋል ።
እንደ አልፑኢ ያሉ አንዳንድ ሰዎች አዲሱ ሕገ መንግሥት አዲስ የአስተዳደር ዘመን ያስገኛል ብለው ቢከራከሩም ሌሎች ግን በዴሞክራሲ ረገድ ያሉት ልማዶች ሊሸረሸሩ እንደሚችሉ በመናገር በጥርጣሬ ዓይን ይታያቸዋል ።

ቱኒዝያ ሌላኛዋ ሩዋንዳ ትሆን ይሆን?
በሀሳብ ደረጃ ቲኒዝያ በአውሮፓ ኅብረት ተቀባይነት ላጡ ተገን   ፈላጊዎች ዋነኛ የመመለሻ ቦታ ልትሆን እንደምትችል ይታመናል ።እንዲህ ያለው ምሳሌ በቅርቡ የብሪታንያና "የሩዋንዳ ዕቅድ"ን ሊተካ ይችላል። ይህም ጥገኝነት ጠያቂዎችን ከአዉሮጳ ወደ አፍሪካ ማዛወርን ያመለክታል ።
ምንም እንኳ የባሕር ዳርቻዋ ወደ ቱኒዚያ ወደ አውሮጳ ለመሻገር  ከሰሜን አፍሪቃና ከሰሃራ በታች ካሉ አገሮች የሚመጡ ስደተኞችንዋነኛ ማስተናገጃ ብትሆንም፤ ይህ ስደተኞችን ወደ ቱኒዝያ የመመለስ ሁኔታ ግን ሊተገበር የሚችል አይመስልም ።
በሚያዝያ ወር መጀመሪያ ላይ የቱኒዚያ ፕሬዚዳንት ካይስ ሰይድ በብሔራዊ የደኀንነት ስብሰባ ላይ ባደረጉት ንግግር ቱኒዚያ ከሰሃራ በታች ለሚገኙ ስደተኞች "ማዕከል ወይም ማቋረጫ አትሆንም" ብለዋል ። በማከልም  "ከአውሮጳ የሚባረሩ ስደተኞችን አንቀበልም" ሲሉም ተናግረዋል ።
 ሰይድ እንዲህ ያለ መግለጫ ሲሰጡ የአሁኑ የመጀመሪያ ጊዜያቸው ባይሆንም ፤ በተለይም የአውሮጳ ኅብረትና ኢጣሊያ በቱኒዚያ በኩል የሚደረገውን ፍልሰት ለመገደብ ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ መሆናቸው ይታወቃል።  ቱኒዚያ ግን ተጨማሪ ስደተኞችን ለማስተናገድ ወይም ወደ አገራቸው ለመመለስ ፈቃደኛ አለመሆኗ ግልጽ ነው።  የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጂዮርጂያ ሜሎኒ ቱኒዚያ "የሩዋንዳ ዕቅድ" እየተባለ የሚጠራውን ስደተኞችን ወደ ቱኒዝያ በግዳጅ የመመለስ ሐሳብ ፕረዚደንት ካይስ ሰይድ ውድቅ ማድረጋቸውን ደግፈውታል ።
ይህ ድጋፍ የመጣው ጣልያን  ከቱኒዝያ ጋር ያላትን አዲስ ስምምነትለአፍሪካ "ማቴይ ዕቅድ" እየተባለ በሚጠራ ማዕቀፍ የ105 ሚሊዮን ዩሮ (111.7 ሚሊዮን ዶላር) ፣ የኢኮኖሚ ዕድሎችን ለማስፋፋትና ወደ አውሮጳ የሚደረገውን ፍልሰት ለመከላከል በአህጉሪቱ ሰፊ ስትራቴጂያዊ ስምምነት ከተስማማች በኋላ ነው ።
እነዚህ ስምምነቶች የተፈረሙት ቱኒዚያ የአውሮጳ ሕብረት ``የትብብር ማዕቀፍ`` ባለው ፕሮግራም ከ1 ቢሊዮን ዩሮ በላይ የገንዘብ ድጋፍ እንድታገኝና የ105 ሚሊዮን ዩሮ ደግሞ መደበኛ ያልሆነ ስደትን ለመግታት የገንዘብ ድጋፍ እንድታገኝ ካደረገች ከስምንት ወራት በኋላ ነው ። እንዲህ ያለው  ሽርክና የስደተኞች ቁጥር በመቀነስ በኩል የተወሰነ ስኬትን ማስመዝገቡን ይነገራል ።
የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ጉዳይ ድርጅት በቅርቡ ያወጣው መረጃ እንደሚያመለክተው  እንደ አውሮጳውያኑ አቆጣጠር ከሚያዝያ15, 2024 ጀምሮ የቱኒዝያ የድንበር ጠባቂዎች 21, 000 ስደተኞችን ወደ አውሮፓ ወደሚወስዱ የባሕር መስመሮች ከመግባታቸው በፊት ተቆጣጥረዋቸዋል። 
በ2023 ከነበረው ተመሳሳይ ወቅት ከሊብያና አልጄርያ ወደ ጣልያን ከገቡ ስደተኞች ጋር ሲነጻጸር በግማሽ ያነሰ ነው። በዚሁ ወቅት የገቡ ስደተኞች ቁጥር 16,000 ያህል ነበር ።
"የአውሮፓ ኅብረት ከቱኒዝያ ጋር ያለው ስምምነት ስደተኞችን  ከአውሮፓ ኅብረት እንዲወጡ ለማድረግ ታስቦ የተዘጋጀ እንጂ ቱኒዚያ ብቻዋን እንዳታደርግ ታስቦ የተዘጋጀ አደለም" ሲሉ በአውሮፓ የውጭ ግንኙነት ምክር ቤት የመካከለኛው ምሥራቅና የሰሜን አፍሪካ ፕሮግራም ሥራ አስኪያጅ ኬሊ ፒቲሎ ለDW ተናግረዋል ።
"የአውሮጳ ሕብረት ከቱኒዝያ ጋር ያለው ስምምነት ስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎች ከአውሮፓ ኅብረት አባል ሐገራት እንዲወጡ ለማድረግ ታስቦ የተቋቋመ እንጂ ከቱኒዝያ ማስወጣት ያለመ አደለም። እነዚህ ስምምነቶች የሚያደርጉት ብቸኛ ነገር የስደተኞችንና ተገን ጠያቂዎችን መብት ገሸሽ እንዲባል ማድረግ ነው። መዋቅራዊ ለሆኑ ጉዳዮች የተሰጠው ትኩረት አነስተኛ ነው፤  እነዚህ ስደተኞች አደገኛ ጉዞዎችን የሚያደርጉት መሠረታዊ የሆኑ ጉዳዮችንና መሠረታዊ የሆኑትን ችግሮች ለመቅረፍ ብዙም አይሞክሩም ። በተጨማሪም  ስደተኞቹ በቱኒዝያ ሲያርፉ ጉዳያቸውን ለመጨረስ የሚያስችላቸውን  ድጋፍ አይሰጡም ። ከስደተኞችና ከስደተኞች አያያዝ ጋር በተያያዘም ስምምነቱ የመንግሥት የስደተኞቹ የሰብዓዊ መብት ሁኔታዎች አያያዝና  ግምት ውስጥ ያስገባ አደለም ። "

የቱኒዝያ ፕረዚደንት ካይስ ሰይድ
የቱኒዝያ ፕረዚደንት ካይስ ሰይድምስል Chokri Mahjoub/ZUMA Wire/IMAGO

ከዚህም በላይ  እ.ኤ.አ በሐምሌ 2021 ፕሬዚዳንት ሰይድ ስልጣን መቆጣጠራቸውን ተከትሎ ፕሬዝደንቱ ብዙ የዴሞክራሲ ተቋማትን ማፍረሳቸው ብቻ ሳይሆን በስደተኞችም ላይ እርምጃ ለመውሰድ መዛታቸውን ተከትሎ ቱኒዚያ ለስደተኞች "ደህና አገር" ሆና ልትታይ እንደማትችል መረጃዎች ያመላክታሉ። ፒቲሎ አክለውም የአውሮጳ ሕብረትና ጣልያን የስደተኞችና ተገን ጠያቂዎች የሰብአዊ መብት ይዞታን አቃለው እንደሚመለከቱት ነው የገለጹት።

በሂውማን ራይትስ ዎች የቱኒዝያ ጉዳይ ዳይሬክተር  ሳልሳቢል ቺሌሊም በዚህ አባባል  ይስማማሉ ።
"ዛሬ በቱኒዚያ  ጥገኝነት ጠያቂዎችና ስደተኞች ገና ባሕር ጠረፍ ከመድረሳቸው በፊት የበብሔራዊ ጥበቃና የድንበር ጥበቃ አባላትን ጨምሮ በፀጥታ ኃይሎች ከባድ በደል ይፈጸምባቸዋል ። በዘፈቀደ ይታሰራሉ ፣ ተገቢ ያላሆነ አያያዝ ይፈጸምባቸዋል ። በተጨማሪም የቱኒዚያ ባለሥልጣናት በሊቢያና በአልጄሪያ ድንበር ላይ የሚገኙስደተኞችንና ጥገኝነት ጠያቂዎችን በሃይል ማስወጣታቸውን ቀጥለዋል ። ይህ ተግባር በአሁኑ ጊዜ የተለመደ ሆኗል ።
ከዚህም በተጨማሪ በአገሪቱ ውስጥ የሚገኙ በርካታ ስደተኞች በጣም ውድ በሆነ የኑሮ ሁኔታ ውስጥ የሚኖሩ ሲሆን ለምሳሌ ያህል ፣ መሠረታዊ የሆኑ ነገሮችንና አገልግሎቶችን ማግኘት በማይችሉበት ሰፋያቕክስ በሚባል አካባቢ የሚኖሩ በርካታ ስደተኞች አሉ ።
ይህ ሁኔታ የፕሬዘዳንት ካይስ ሰይድ እርምጃ ውጤት ቢሆንም ከአውሮፓ ህብረት የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ጋር የተቆራኘ ነው። ይህ ተግባር በቱኒዝያ ያሉ ስደተኞችን፤ የአውሮጳ ሕብረት  ያወጣቸውን የሰብአዊ መብት  እሴቶችን በመጣስ ለመቆጣጠር የሚደረግ ተግባር ነው።"

ከቱኒዝያ ወደ ጣልያን ከሚሻገሩ ስደተኞች በከፊል
ከቱኒዝያ ወደ ጣልያን ከሚሻገሩ ስደተኞች በከፊልምስል AP


ቱኒዚያም ብሔራዊ የስደት ህግጋት የሌላት ከመሆኑም በላይ ለስደተኞች ሕጋዊነትን የሚፈቅድ ወይም ሰዎች እንዲሠሩ የሚፈቅድ ሥርዓት የሌላት አገር መሆኗንም በሂዩማን ራይትስ ዎች የስደተኞችና ስደተኛ የመብት ተመራማሪ የሆኑት ሎረን ሴበርት ተናግረዋል ።

"እናም ከዚህም በላይ፤  አዎን ፣ በሀገሪቱ ውስጥ ለተመዘገቡ ስደተኞችም ሆነ ለተገን ጠያቂዎች በጣም አስጊ የኑሮ ሁኔታ የመኖሩ ጉዳይ ጭምር አለ ። የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ጉዳይ ድርጅት ፣ ሁሉንም የተመዘገቡ ጥገኝነት ጠያቂዎችንና ስደተኞችን ሰብዓዊ ፍላጎታቸውን አሟልተው ለመርዳት የሚያስችል በቂ ሀብትና  አቅም የለውም ። ስለዚህ ብዙ ስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎች መጠለያ የሌላቸውና በጎዳናዎች በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ የሚገኙ ናቸው ። ይህ ደግሞ  በተለይ ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ አገሮች የመጡ የውጭ አገር ዜጎች በአገሪቱ ውስጥ እያጋጠማቸው ያለ ተጨማሪ ችግር ነው ። "

በቱኒዝያ ከሚገኙ ስደተኞች በከፊል
በቱኒዝያ ከሚገኙ ስደተኞች በከፊልምስል Hasan Mrad/ZUMA Wire/IMAGO

በአሁኑ ጊዜ በቱኒዝያ 12,000 የሚያህሉ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ ኮሚሽን ሥር የተመዘገቡ ስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎች ይገኛሉ ። የጀርመን ሃይንሪክ ቦልት ፋውንዴሽን በቱኒዝ ቢሮ ዲሬክተር የሆኑት ሄይክ ሎሽማን " ከሰሃራ በታች ወደ 80,000 የሚጠጉ ስደተኞች የተሻለ የአየር ሁኔታ ለማግኘት ሲሉ ከሰፋቕስ በስተ ደቡብ በሚገኘው የወይራ ተክል ውስጥ እየጠበቁ ናቸው" ሲሉ ተናግረዋል ።

“አዎ፣ በእርግጥ እስከ 80,000 የሚደርሱ ከሰሃራ በስተ ደቡብ ያሉ ሐገራት ስደተኞች አሁን በቱኒዚያከስፋቅስ በስተደቡብ በሚገኙ የወይራ እርሻዎች ውስጥ ሆነው የተሻለ የአየር ሁኔታን እየጠበቁ መሆናቸውን ያውቃሉ።  እናም በጸደይ ወራት የሚደረግ ስደት እንደገና መጤን ያለበት ነገር ነው። የቱኒዚያ ዜጎች ወደ ጣሊያን በህጋዊ መንገድ የሚገቡበት መንገድ ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ተደርጎ በሌላ በኩል ደግሞ በጣሊያን ሌላኛው ጫፍ ህገ ወጥ ስደተኞችን መቀበል አልፈለጉም።“
በደቡብ በኩል በምትገኘው አል ጂዳሪያህ ያለው ሁኔታም ይበልጥ አስከፊ እየሆነ መምጣቱን የቱኒዚያ የሰብዓዊ መብቶች ምርምር ኃላፊ ሙስጠፋ አብደል ካቢር ይገልጻሉ ።
አካባቢው በጣም ርቆ የሚገኝ ከመሆኑም በላይ የመኖሪያና የመስሪያ ቦታ እጦት የሚታይበት ነው።  ቢሆንም  ግን በመቶዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች ወደዚህ መጥተው ብቻቸውን እንደሚኖሩ ለDW ተናግረዋል ።
ቱኒዝያ በመጪው ጥቅምት ወር ላይ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የምታካሂድ ሲሆን  ፕረዚደንት ሰይድ በአገሪቱ ሕዝብ እያደገ የመጣውን የስደተኛ ጠል አስተሳሰብን ጫና ሰጥተው ለማሻሻል ይጥራሉ ተብሎ አይታሰብም። ከዚህ ይልቅ የአገሪቱን የኢኮኖሚ ቀውስ በመፍታትና የሕዝብን ቀልብ ለመሳብ እንደሚጥሩ ምንም ጥርጥር የለውም ።

 ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር 

ነጋሽ መሐመድ