1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የበዓል መዳረሻ ወጎች ፣ ልማዶች እና ትዝታዎቻቸው

ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 26 2016

በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በታላቅ ስነስርዓት የሚከበረው የኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ትንሳኤ በነገው እለት እሁድ በመላው ኢትዮጵያ ይከበራል፡፡ በዓሉ ወዳጅ ከወዳጅ፤ ቤተሰብን ከቤተሰብ የሚያገናኝ የአብሮነት በዓል ከሚባልላቸው ተጠቃሽ ነው

https://p.dw.com/p/4fVQ9
Äthiopien Kiremu
ምስል Privat

የትንሳኤ በዓል ዋዜማ እና የበዓል አቀባበል አንድምታው በምዕራብ ኦሮሚያ

የበዓል መዳረሻ ወጎች ፣ ልማዶች እና ትዝታዎቻቸው

በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በታላቅ ስነስርዓት የሚከበረው የኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ትንሳኤ በነገው እለት በመላው ኢትዮጵያ ይከበራል፡፡

በዓሉ ወዳጅ ከወዳጅ፤ ቤተሰብን ከቤተሰብ የሚያገናኝ የአብሮነት በዓል ከሚባልላቸው ተጠቃሽ  ነው፡፡

ይሁንና በሀገሪቱ ውስጥ በሚታየው የጸጥታው መደፍረስ ምክንያት ይህንን ቀን በትዝታ ብቻ የሚስታውሱ በርካቶች ናቸው፡፡

ዛሬ በመላው ኢትዮጵያ በሁሉም የክርስትና እምነት ተከታዮች በሚከበረው የትንሳኤ በዓል ዋዜማ ላይ እንገኛለን፡፡ በተለይም ከሁለት ወራት ጾም በኋላ በዓሉን ለሚያከብሩት የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች ትንሳኤ እጅጉን የሚጠበቅ የራሱ የሆነ ድባብም ያለው ነው፡፡

በዚህ በዓል የሩቅ ቤተዘመድ ከቅርቡ፣ ልጅ ከቤተሰቡ እና ወዳጅ ከወዳጁ ብዙ ርቀትም ተጉዘው መገናኝት፤ ለበዓሉም ቤት ያፈራውን አብሮ መቋደስ ሲወርድ ሲወራረድ የመጣ ዘልማድም ጭምር ነው፡፡ ይሁንና በአገሪቱ ግጭት አለመረጋጋቱ ላለፉት ጥቂት ዓመታት በተስተዋለባቸው አከባቢዎች የጸጥታ ስጋቱ ሰፍኗልና ይህ እንደተለመደው መገናኘቱ፤ በዓልን ከቅርብ ሩቁ ጋር አብሮ ማሳለፉ የተገታ መስሏል፡፡

በዓለ ስቅለትና የትንሳኤ ገበያ

የኑሮ ውድነት ጫና

በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ወለጋ ዞን ኪረሙ ወረዳ ያለፉትን ሶስት-አራት ዓመታት በግጭት ውስጥ ያሳለፉ ሰለሞን የተባሉ ነዋሪ ከግጭት ማግስት ነገሮች ወደ ነባር ይዞታቸው እንዲመለሱ ጥረቶች ቢታዩም አሁንም ጊዜ ሳይፈልግ አይቀርም ይላሉ፡፡ አቶ ሰለሞን የበዓሉን አከባበር ዝግጅት ተጽእኖ ከተወደደው የግብዓቶች አቅርቦት ይጀምራሉ፡፡

“የበዓል መዳረሻ ድባቡ ምንም አይልም ደህና ነው፡፡ ግን እኮ ፍየልና በግ የመሳሰሉ የበዓሉ ማድመቂያዎች እዚህ ውድ ነው በጣም፡፡ ምክኒያቱ ደግሞ በግጭቱ ምክኒያት ሰው በሙሉ ወደ ከተማ ሸሽቶ ምርቱ የለምና አቅርቦቱ እጅጉን አናሳ ነው” ብለዋል፡፡

ሰለሞን አስተያየታቸውን ቀጠሉ እንደ ተለመደው በዓልን በጥሩ መንፈስ ማክበር አሁን ላይ ባይታሰብም፤ አከባቢያቸው በግጭት ከተናደባቸው ካለፉት አስከፊ ትዝታቸው በተሻለ አሁን  ተስፋዎች መታየታቸውን ያስረዳሉ፡፡ “እሱ እንኳን አይታሰብም፡፡ በዚህ ከኪረሙ የሚያልፍ የለም፡፡ በሌላኛው አቅጣጫ ደግሞ እኔ ከምገኝበት ሀሮ ቀበሌ ወደ አጎራባች ከተማ አገምሳ እንኳ መዝለቅ አስጊ ነው፡፡ እርጉዝ እንኳ ታማብህ ይዘህ ወጥተህ ሌላ ደህና ከተማ ማሳከም ብታስብ ትፈተናለህ፡፡ እንኳን በዓል እንደጥንቱ አብሮ ማክበር የቅርብ ዘመድ ሞቶብህ 60 ኪ.ሜ ገደማ ተንቀሳቅሰህ መቅበር ፈተና ነው” ይላሉ፡፡

የስቅለት በዓል አከባበር በአዲስ አበባ

ነገር ግን ብለዋል አስተያየት ሰጪው፡ በቅርቡ በተፈጠረው አንጻራዊ መረጋጋት ወደ ከተማ የሸሸው የገጠሩ ማህበረሰብ ተስፋ ኖሮት ወደ ገጠር ቀየው ተመልሶ እርሻውን ወደ ማረስ መመለሱ ትልቅ እፎይታ ነው፡፡ የትንሳኤ በዓል በጉልህ እንደምክበርም በማንሳት ለዚሁም ማህበረሰቡ ባለው ሽር ጉድ እያለ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ሁሉም ወዳጅ ዘመድ ተሰባስቦ በፍጹም ነጻነትና ደስታ የሚያከብረው በዓል ግን ለማክበር በዚህ አከባቢ ጊዜው ገና ይመስላል፡፡ አቶ ሰለሞንም ይህን አረጋግጠውልናል፡፡ ሆኖም ግን ከዚህ በፊት በህብረተሰብ መካከል የተፈጠረው ጥርጣሬና የብሔር ግጭት በሁሉም ማህበረሰብ የአብሮነት ፍላጎትና ስህተቶችን መረዳት ተስፋው አብቧል ባይ ናቸው፡፡

የትንሳኤ በዓል አከባበር በኦርቶዶክስ እና ካቶሊክ አብያተ ክርስቲያናት 

የፀጥታው ስጋት የደቀነው እንቅፋት

ከዚሁ በግጭት ውስጥ ከቆየው ዞን ሌላኛው ወረዳ ጊዳ አያና አስተያየታቸውን የሰጡን ነዋሪም ሀሳባቸውን አከሉ፡፡ እንደ ወትሮውም በዓሉ ጊዜውን ጠብቆ መምጣቱን ብገነዘቡትም የሚላስ የሚቀመስ አጥተው በዓሉን ለማሳለፍ የተዘጋጁትን በርካቶች ያውቁአቸዋል፡፡ “ይህ አከባቢያችን እጅግ ጥሩ አከባቢ ነበር፡፡ በጉ፣ ፍየሉ፣ ከብቱ ዶሮው ሁሉም ይመረት ነበር እኛ ጋ፡፡ ተፈጥሮ በጸጋ የባረከችው አከባቢ ነበር፡፡ ፈጣሪ ምንም አልነሳንም፡፡ አሁን ግን ያ ሁሉ የለም፡፡ የነበረው ግጭት በማህበረሰቡ እጅ የነበረውን አውድሟል፡፡ ህዝቡ በእጅ ላይ የለው የሚገዛበት ነገር ይቸግረዋል፡፡ እና ሳይቀምስ እንኳ በዓሉን የሚያሳልፍ ይኖራል፡፡ ህብረተሰቡ አሁን ቀን የሚገፋው በእርዳታ ነው፡፡ እናም በዓል አይመስልም እኛጋ፡፡ በጣም ነው የሚከፋን፡፡ አያት ቅድመአያታችን አይተው የማያውቁ ዶፍ እኮ ነው የወረደብን፡፡ ከችግር ጋር ተገናኝተን አናውቅም ነበር፡፡ ድርቅ አናውቅ ርሃብ የለም ነበር፡፡ አሁን ግን ማህበረሰባችን አይቶ በማያውቅ ችግር ይሰቃያል፡፡ ከእጁ ያለው ጠፍቶበታል፡፡ ውሎ አዳር የለው፡፡ ታውቃለህ ስታስታውሰው አገር ጥለህ ጥፋ ያስብላል በጣም ነው የሚያሳዝነው” ሲሉ ሃሳባቸውን አብራርተዋል፡፡

"ካለፉት በዓላት የተሻለ ድባብ አለ"

ወትሮም እንደ ትንሳኤ ያለው አውዳመት በኢትዮጵያ ቤተሰብን በእጅጉ የሚያገናኝ ነውና ልጅ ከከተማ ወደ ገጠር እየሄደ ቤተሰብ መጠየቅም ወግ ነበር፡፡ አሁን ለዚህ እንዳልታደሉ የሚገልጹና የቤተሰቦቻቸውን ደጅ ከረገጡ ዓመታት ያስቆጠሩ ስፍር ቁጥር የላቸውም፡፡ ፖለቲከኛ መረራ ጉዲና ከዚሁ ጋር ተያይዞ ከዚህ በፊት ለዶይቼ ቬለ በሰቱት አስተያየት “እኔ ኮ አምቦ ቤተሰቦቼን ለመጠየቅ ከሄድኩ ሁለት ዓመት አልፎኛል” በማለት የጸጥታውን ብርቱ ፈተና አስረድተዋል፡፡

ሥዩም ጌቱ

ታምራት ዲንሳ