1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአፍሪቃውያን ተስፋ ከመርከቦቹ ይልቅ በራስ ቀዬ ቢሆን

ቅዳሜ፣ ነሐሴ 14 2014

አፍሪቃውያኑ ጥገኝነትን እየቀነሱ የበለጠ መቋቋምን ማምጣት እንዴት ይቻላቸው ይሆን ? ከዚሁ ጎን ለጎን እንደ ኖንሴዶ ቩቱላ ያሉ ተመራማሪዎች ጥቅም ላይ ያልዋሉ ሰፋፊ የእርሻ መሬቶች ጥቅም ላይ እንዲውሉ በማድረግ አፍሪካ ከውጪ ከሚላኩላት መርከቦች ጥገኝነትን እንዴት መቀነስ እንደምትችል መንገድ ማፈላለጋቸው ተስፋ ሰጭነቱን አሳይቷል።

https://p.dw.com/p/4FouE

የአፍሪቃውያን ተስፋ ከመርከቦቹ ባሻገር ፤ ዛምቢያውያን እና የነዳጅ ድጎማው

በመጨረሻም ነገሮች መስመር መያዝ ጀምረዋል። በሩስያ እና ዩክሬን መካከል እየተካሄደ ባለው ጦርነት ምክንያት ዝግ ሆኖ የቆየው የጥቁር ባህር ዳግም ተከፍቶ የምግብ እህል የጫኑ መርከቦች ከዩክሬን ወደቦች መውጣት መጀመራቸው ዓለማቀፉን ማህበረሰብ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ተንፈስ አድርገዋል።  ከባለፈው የሐምሌ ወር አንስቶ ከሃያ በላይ መርከቦች በቆሎ፣ ስንዴ እና የሱፍ ዘይት  ጭነው ከዩክሬን ወደቦች መነሳታቸውን  ሩስያ ፣ዩክሬን እና ቱርክ በተባበሩት መንግስታት አስተባባሪነት የመሰረቱት የጋራ ማስተባበሪያ ማዕከል አስታውቋል። 
የመርከቦቹ ጉዞ መጀመር በተለይ እንደ ምስራቅ አፍሪቃ ላሉ በዓለም ላይ ለከፋ ድርቅ እና ረሃብ ለተጋለጡ ሀገራት መልካም ነገር ይዞ መጥቷል። በቀጣናው ባሉ ሃገራት ባለፈው የሰኔ ወር 89 ሚሊዮን ሕዝብ ለከፋ የረሃብ አደጋ መጋለጣቸውን በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የዓለም የምግብ ፕሮግራም አስታውቋል። በአፍሪቃ ቀንድ ለአራት ተከታታይ ዓመታት ዝናብ ያልዘነበባቸው አካባቢዎች መኖራቸውን የጠቀሰው ዓለማቀፉ ድርጅት ካለፉት ዓመታት አንጻር ቀጣዮቹን ዓመታት ችግሩ የከፋ ሆኖ እንዳይቀጥል ስጋት አለኝ ብሏል። በሌሎች የአፍሪቃ ክፍሎች እና በመካከለኛው ምስራቅ ሃገራትም እንዲሁ የምግብ ዋጋ ጣርያ መንካቱ ከምግብ ጋር የተያያዘው ዓለማቀፍ ቀውስ በጥቂት ሃገራት ብቻ የተወሰነ ላለመሆኑ ማሳያ ሆኗል። እንደዚያም ሆኖ ግን ከዩክሬን ወደቦች ጉዞ እንደጀመሩ ከተነገራለቸው መርከቦች ውስጥ ወደ ምስራቅ አፍሪቃ ጉዞ የጀመረው ገና አንድ መርከብ ብቻ ነው። 
በኬፕታውን የግብርና እና ክልላዊ ውህደት ባለሞያ  የሆኑት ኖንሴዶ ቩቱላ እንደሚሉት አፍሪቃውያን አሁን ከገጠመን የምግብ እህል እጥረት ብዙ ልንማር ይገባል ባይ ናቸው።  
“ንግድን እስከምናበረታታ ድረስ በአንድ የዓለም ክፍል ላይ በአንድ የተወሰነ ምርት ላይ በጣም ጥገኛ መሆን የለብንም፣ ይልቁኑ በአንደኛው የዓለም ክፍል አንድ ነገር ሲከሰት ቢያንስ ሌሎች የመሠረታዊ የምግብ ሸቀጣ ሸቀጦችን ለማግኘት ሌሎች አማራጮችን ለማጤን ጥረት ማድረግ አለብን። ”

Ukrainischer Weizen für Afrika | Transportschiff "Brave Commander"
ምስል NurPhoto/picture alliance

በኔልሰን ማንዴላ የህዝብ አስተዳደር ትምህርት ቤት አጥኚ የሆኑት እኚሁ ምሁር ለዶይቼ ቬለ በሰጡት ሃሳባቸው አህጉሪቱ ለበርካታ ጉዳዮች ተጋላጭ መሆኗን ነው ያነሱት 
«ዓለማቀፋዊ አካባቢያዊ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ተጋላጭ መሆናችን በተለይ እና አፍሪቃውያንን  ምን ያህል ሊጎዳን እንደሚችል ከደረሰብን ልንማር ይገባል። » 
ብሬቭ ኮማንደር የተሰኘችው መርከብ ከ23,000 በላይ ሜትሪክ ቶን ስንዴ ጭና በቱርኳ ኤስታንቡል መልህቋን ጥላለች። መርከቧ ወደ ጂቡቲ ነው የምታቀናው። እህሉ በኢትዮጵያ 1,5 ሚሊዮን እርዳታ ፈላጊዎችን ለአንድ  ወር አካባቢ ለመመገብ እንደሚያስችል በጀርመን፣ ኦስትሪያ እና ሊችተንስታይን የአለም የምግብ ፕሮግራም ዳይሬክተር ማርቲን ፍሪክ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።
በቀጣዮቹ ቀናት ምን ያህል መርከቦች ከዩክሬን ወደቦች ይወጣሉ ለሚለው ጥያቄ ዳይሬክተሩ ሲመልሱ ያለውን ዓለማቀፋዊ ሰፊ ፍላጎት ለማሟላት ጥረቶች እየተደረጉ መሆናቸውን ይገልጻሉ።  
" ፍላጎቱ ሰፊ ነው፤ በአሁኑ ጊዜ ተጨማሪ ገንዘብ ለመሰብሰብ ከዋና ለጋሾቻችን ጋር በሁሉም አማራጮች እየተነጋገርን ነው።"  
የምስራቅ አፍሪቃ ሃገራትን በተለየ ሁኔታ ያነሱት ማርቲን ፍሪክ በ40 ዓመታት ታሪክ ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ አካባቢውን ያጠቃው የከፋ ድርቅ የተለየ ትኩረት እንዲሰጥበት አድርጓል ይላሉ ። 
"ህዝቡን ለመርዳት በምንችለው አማራጮች ሁሉ ገፍተን መቀጠል ይኖርብናል። በእርግጥ የገንዘብ እና የምግብ እጥረት አለብን ፣ነገርግን በጣም ተጋላች የሆኑትን ቅድሚያ ለመስጠት  እና ለመርዳት ጥረት እናደርጋለን። »
ከዩክሬን የምግብ እህሎችን ጭነው የሚወጡ መርከቦች በከፋ ችግር ውስጥ ካለችው አፍሪቃ ይልቅ ለአየር ላንድ ፣ ጣልያን እና ቻይና ቅድሚያ መስጠታቸው ጥያቄ አስነስቷል። ምክንያቱ ደግሞ ከዩክሬን እህል ጭነው ከወጡ ከሃያ ገደማ መርከቦች ወደ ምስራቅ አፍሪቃ ጉዞ የጀመረው አንድ መርከብ ብቻ በመሆኑ ነው ፤ እስቲ ሃሳቡን ገፋ አድርገን እንመልከት። 
በጥቁር ባህር አካባቢ ያለውን የመርከቦች እንቅስቃሴ ወደ መደበኛነት የመመለስ ተስፋ እንደሚታይበት የሚገልጹት ዋና ዳይሬክተሩ ነገር ግን አሁንም ቢሆን ሌሎች እንቅፋቶች መኖራቸውን አልሸሸጉም ። 
«የመርከቦች እንቅስቃሴ ወደ መደበኛው መስመሩ ቢመጡም አሁንም አሳሳቢ ሆኖ የሚዘልቀው ጉዳይ ለመርከቦቹ  የመድን ዋስትና እና ተያያዥ ጉዳዮች መጠየቃቸው አይቀርም። ኩባንያዎቹ በንግድ መስመሩ ላይ  ስጋት ሲፈጥሩ ቆይተዋል። » 
እንደዚያም ሆኖ ግን የመርከቦቹ እንቅስቃሴ መጀመር በባሕር መጓጓዣ ላይ የ10 ከመቶ የዋጋ ቅናሽ አሳይቷል። ምንም እንኳ ከአምናው የተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር አሁንም ድረስ የ16 ከመቶ ብልጫ ቢኖረውም። 
አንዳንዶች ብሬቭ ኮማንደር የተባለችው መርከብ ብቻ እህል ጭና ወደ አፍሪቃ ጉዞ መጀመሯን በምሬን ያነሳሉ። ለዚያውም እንደነ አየርላንድ ፣ ጣልያን እና ቻይናን የመሳሰሉ ሃገራት ቅድሚያ ከወሰዱ በኋላ መሆኑ ደግሞ ጉዳዩን አስገራሚ ብቻ ሳይሆን የሚያበሳጭ ሆኖ ነው የተገኘው። ለዚያውም የአንዷ መርከብ ወሬ ብዙ ከተራገበ በኋላ። እንደዚያም ሆኖ ግን ባለስልጣናቱ ይህን እንደ ችግር አይመለከቱትም ። መርከቦችን በብዛት ለማሰማራት መሟላት ያለባቸው ውሎች እንዳሉ ነው የሚጠቅሱት ። 
በጎቲንገን ዩኒቨርሲቲ የግብርና ኢኮኖሚ ፕሮፌሰር የሆኑት ስቴፋን ቮን ክራሞን-ታባዴል  የንግድ እንቅስቃሴው ቀጥተኛ ያልሆነ ጠቀሜታ እንዳለው ይናገራሉ  ከዩክሬን የሚወጣ እያንዳንዱ መርከብ  በአፍሪካ እና በተባበሩት መንግስታት የጅምላ አቅራቢዎች ብዙ ስንዴ እንዲገዙ ያስችላቸዋል፤ ይህ ደግሞ የዓለም የገበያ ዋጋን ለመቀነስ እንደሚረዳ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። 
"በመጀመሪያ መርከቦቹ ለረጅም ጊዜ በፊት አስቀድሞ የታዘዘውን ጭነት መላክ አለባቸው።"
ሩስያ በኃይል ከተቆጣጠረቻቸው የዩክሬን አካባቢዎች በክምችት ያሉ የእህል ምርቶችን ዘርፋለች የሚለው ዜና የብዙዎችን ቀልብ የያ,ዘ ነበር። በእርግጥ ሩስያ ይህንኑ በተደጋጋሚ ስታስተባብለው ቆይታለች። እውነት ግን ሩስያ የዩክሬንን እህል ዘርፋ ይሆን ? ዘገባው ጥያቄውን ያነሳና ይቀጥላል። 
መርከቦች ከዩክሬን ወደቦች እህል ጭነው መውጣት የሚችሉት ዩክሬን እና ሩስያ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና ከቱርክ ጋር በተናጥል ከስምምነት በደረሱት መሰረት ብቻ ነው የሚሆነው። አፈጻጸሙ ደግሞ ከዩክሬን ወደቦች የሚነሱት መርከቦቹ በቱርኳ ኢስታንቡል ከተማ ውስጥ የጋራ የደህንነት ፍተሻ ከተደረገላቸው በኋላ ይሆናል። ይህም መርከቦቹ እንዲያጓጉዙ የተፈቀደላቸውን ጭነት ብቻ ስለመጫናቸው ማረጋገጫ ያሰጣቸዋል። 
ሩሲያ በዩክሬን ላይ ባካሄደችው ጦርነት በመጀመሪያዎቹ ወራት በጦርነቱ እና በባህር ላይ ሲደርሱ በነበሩ ፍንዳታዎች ምክንያት የእህል ጭነት ማጓጓዝ  የማይቻል ነበር ። ነገር ግን ኪዬቭ በይፋ ክሷን ማሰማት የጀመረችው ስንዴ ለዓለም ገበያ ማቅረብ አልቻልኩም ብቻ አልነበረም ። ይልቁኑ ሩስያ በክምችት ያለውን እህሌን ዘርፋ ለራሷ አሳልፋ ሸጣለች ስትል ብርቱ ክስ ስታሰማ ቆይታለች። 
ቮን ክራሞን-ታባዴል እንደሚሉት  በሩሲያ በተያዙ በእነዚሁ የዩክሬን አካባቢዎች የሚገኙ የአካባቢ ባለስልጣናት ይህንኑ ስራቸውን ለመደበቅ እንኳን አይሞክሩም ። ከጭነት መርከቦች የሚገኘው የመጓጓዣ መረጃዎች ተጨማሪ ማስረጃዎችን ይሰጣል የሚሉት የግብርና ኤኮኖሚ ባለሞያው  በተለምዶ የንግድ መርከቦች በማንኛውም ጊዜ የቦታ መረጃቸውን ይፋ ማድረግ ሲኖርባቸው እጅግ አስደናቂ ቁጥር ያላቸው የሩሲያ መርከቦች የሚገኙበትን  ቦታ የሚያሳውቅ መጠቆሚያ መሳርያ ማጥፋታቸውን ታባዴል ተናግረዋል።
«በእርግጥ ስንዴውን በማየት ከየት እንደመጣ ማወቅ ይቻላል» የሚሉት ባለሞያው ስንዴው ከሚደርስበት ሀገር ርቀት እና ይህንኑ ለማጥራት  ዋጋው ውድ ስለሚሆን ሂደቱ አዋጭ እንደማይሆን ነው ።
"ይህ አሰራር ብዙ ወጪ የሚጠይቅ ነው - እና ከጥቁር ባህር አካባቢ የሚገኘው እህል በተቻለ ፍጥነት ለተቸገሩ ሸማቾች እንዲሰራጭ የምንፈልግበትን ጊዜ  ያደናቅፋል።"
በተጨማሪም የኤክስፖርት ፍሰቱ ለቀጣዩ የመኸር ወቅት የእህል ጎተራዎችን ለማጽዳት ረድቷል፡ በዚህ ጊዜ ቮን ክራሞን-ታባዴል እንደሚሉት በየወሩ ስድስት ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን መውጣት ነበረበት።
ያም ሆነ ይህ ግን የስንዴው የወጪ ገበያ ፍሰት  በየወሩ ከየመጋዘኑ ስድስት ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን እህል መውጣት ይጠበቅበት እንደነበር የጠቀሱት ባለሞያው ሂደቱ ቢሳካና የወጭ ገበያው መስመር ቢይዝ የእህል ጎተራዎችን በማጽዳት ለቀጣዩ የመኸር ወቅት ዝግጅት እንዲደረግ ሊረዳ እንደሚችል ሳይጠቅሱ አላለፉም።
ነገር ግን አንዳንድ የአፍሪቃ ሃገራት ከሩስያ ጋር መልካም ግንኙነት ስላላቸው ለችግራቸው መቀነሻ የሚሆን ስንዴ ቢመጣላቸው ያለ አንዳች ቅሬታ ሊቀበሉት እንደሚችሉ ነው ዘገባው የሚያትተው። 
እናስ አፍሪቃውያኑ ጥገኝነትን እየቀነሱ የበለጠ መቋቋምን ማምጣት እንዴት ይቻላቸው ይሆን  ?
ከዚሁ ጎን ለጎን እንደ ኖንሴዶ ቩቱላ ያሉ ተመራማሪዎች  ጥቅም ላይ ያልዋሉ ሰፋፊ የእርሻ መሬቶች ጥቅም ላይ እንዲውሉ በማድረግ  አፍሪካ ከውጪ ከሚላኩላት መርከቦች ጥገኝነት እንዴት መቀነስ እንደምትችል መንገድ ማፈላለጋቸው ተስፋ ሰጭነቱን አሳይቷል። ከውጭ የሚላከው ስንዴ ቀላል ግምት የማይሰጠው ቢሆንም አንዳንድ ሃገራት ተስፋ ሰጭ ምልክት ማሳየታቸውን ተመራማሪዋ ይናገራሉ። 
"አፍሪካ ውስጥ ከሚመረተው ስንዴ አንፃር ብዙ ነው። ነገር ግን መላውን አፍሪካ ለመመገብ በቂ አይደለም።ለምሳሌ እንደ ኢትዮጵያ፣ደቡብ አፍሪካ፣ታንዛኒያ እና ናይጄሪያ ያሉ አንዳንድ አገሮች ስንዴ እያመረቱ ነው። ነገር ግን  የተቀረውን አፍሪካ ለመመገብ በቂ አይደለም"
ብዙውን ጊዜ ስንዴ ለዳቦ እና  ፓስታ ማምረቻነት  ስለሚውል ፍላጎቱ ከፍተኛ ነው። የአፍሪካ የስንዴ ገበሬዎች በመስኖ ወይም ሙቀትን የሚቋቋም ዘሮችን በመጠቀም ምርታቸውን ማሳደግ ይገባቸዋል። ነገር ግን ይህ የረጅም ጊዜ መፍትሄ ብቻ ነው ሊሆን የሚችለው።
እስከዚያው ድረስ ግን ይላሉ ቩቱላ ፤ በስንዴ መሸፈን ባልተቻለባቸው ቦታዎች እንደ ካሳቫ በመሳሰሉት ጤነኛ እህሎች እና ሙቀትን የሚቋቋም ሀረጎችን እንዲተካ ምክረ ሃሳብ ያቀርባሉ።  “ምርቱ የሰዎችን ፍላጎት ያማከለ መሆን አለበት። ለምሳሌ በመካከለኛው እና በምዕራባዊ  የአፍሪቃ ክፍል ጥቅም ላይ ይውላል፤ በደቡባዊ አፍሪካ ግን ብዙም አይደለም፣ ተቀነባብሮ ከቀረበ ግን ምትክ ሆኖ ሊያገለግል ይችላል፤ እንዲሁም  በአመጋገብ ይዘቱ መቶ በመቶ አልሚ ነው።»
ነገር ግን አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ  በአፍሪካ ለተስፋፋው ረሃብ ካሳቫ መፍትሄ ላይሆን ይችላል። ረሃብ ጊዜ አይሰጥም ። ለዚህ ነው በረሃብ ውስጥ የሚገኙ የቀጣናው ሃገራት  አይኖች የጅቡቲ የባህር ዳርቻ አድማስ የሚያተኩሩት ።  የዓለም የምግብ ፕሮግራም ባልደረባ ማርቲን ፍሪክ አሁንም በአንድ ነገር ተስፋ ያደርጋሉ።  ከዩክሬን ወደቦች ተጭነው  ለዓለም ገበያዎች እንደሚሰራጩ በሚጠበቁት መርከቦች  ። ይቀጥል ይሆን? ዘላቂ አፍሪቃዊ መፍትሔ ከአፍሪቃውያን ያሻል ፤ ጊዜያዊውን ግን ዓለማቀፉ ርብርብ ግድ ይላል። 

Symbolbild I Indien Weizen
ምስል abaca/picture alliance
Äthiopien Tigray Konflikt Symbolbild
ምስል Eduardo Soteras/AFP/Getty Images
Äthiopien Tigray Konflikt Symbolbild
ምስል Eduardo Soteras/AFP/Getty Images
Ukrainischer Weizen für Afrika | Weizenmehl auf dem Markt in Mogadishu
ምስል Farah Abdi Warsameh/AP/picture alliance
Äthiopien Tigray Konflikt Symbolbild
ምስል Eduardo Soteras/AFP/Getty Images
Ukrainischer Weizen für Afrika | Hafen von Djibouti
ምስል XinHua/picture alliance

በዓለማቀፉ የነዳጅ ዘይት ዋጋ ላይ መጠነኛ ቅናሽ ማሳየቱን ተከትሎ በዚህ ወር በዛምቢያ የነዳጅ ዋጋ ቅናሽ አሳይቷል። የኢነርጂ ባለሞያው ጆንስተን  ቺኩዋንዳ እንደሚሉት የሀገሪቱ የመገበያያ ገንዘብ ከዶላር አንጻር መጠነኛ መሻሻል ማሳየቱ ለዚህ አንዱ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ነው። 
«መንግስት በአገር ውስጥ ያለውን የምንዛሪ ለውጥ ተጠቅሞበታል።  ለዚህም ነው በከፊል የነዳጅ ዋጋ እንዲቀንስ የተደረገው። ምክንያቱም የሀገር ውስጥ ምንዛሪ ጨምሯል ፤ ነገር ግን በአለም አቀፍ ገበያ ላይ ዋጋው ከወራት በኋላ አሁን ባለበት ላይሆን እንደሚችል አስቀድመን መገመት እንችላለን።» 
ዛምቢያ በነዳጅ ዋጋ ላይ ባደረገችው የዋጋ ቅነሳው በዛሚባ ላሉ አሽከርካሪዎች እና ሌሎች የነዳጅ ተጠቃሚዎች በጣም አስፈላጊ ነው የተባለለት  እፎይታ እንደሰጣቸው ነው የተነገረው ። ቺኩዋንዳ እንደሚሉት እርምጃው በዚህ ወር ብቻ ለሸማቾች በድምሩ ከ27 ሚሊዮን ዶላር በላይ ታድጓል።
"ይህ ለሸማቾች ትልቅ ቁጠባ ነው ይዞላቸው የመጣው ። ነገር ግን አሁንም ቢሆን የነዳጅ ዋጋው በጣም ከፍተኛ ነው። አሁንም ከፍተኛ በመሆኑ መንግሥት የነዳጅ  ዋጋን ለመቀነስ የሚያደርገውን ጥረት እንዲቀጥል ማበረታታት እፈልጋለሁ."
ነገር ግን እንደዚያም ሆኖ ሁሉም ዜጎች የነዳጅ ዋጋ መቀነስ አጋዥ ሆኖላቸው አላገኙም። ብዙዎች ጣሪያ የነካውን የሸቀጦች ዋጋን የመቀነስ አዝማሚያ በጭራሽ የለውም  የለውም ሲሉ ምሬታቸውን ይገልጻሉ።
የሜሪ ሙሃሊዮ ቤተሰቦች በመዲናዋ ሉሳካ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ክፍለከተሞች  ከምትጠቀሰው  ካቫታ በሚገኘው ቤታቸው በልብስ ማጠቢያ  የስራ መስክ ላይ ተሰማርተዋል።  ከአገር ውስጥ ገበያ የልብስ ማጠቢያ ሳሙና፣ የማሸጊያ እና  ሌሎች ምርቶችን መግዛት አለባቸው።
" የእኛ ዋጋ ያው ነው ፤ እኛ ዋጋችንን መጨመር አንችልም። በገበያ ላይ ያሉትን ነገሮች ዋጋ ካልቀነሱ በስተቀር እኛ ዋጋችንን መለወጥ አንችልም።"
የዛምቢያ ኢነርጂ ተቆጣጣሪ የነዳጅ ዋጋን ካለፈው የጥር ወር ጀምሮ በየወሩ እየከለሰ ሲሆን ይህም የሀገሪቱ መገበያያ ገንዘብ ክዋቻን ከዶላር አንጻ በማመጣጠን  የነዳጅ እና የመሰረታዊ ፍጆታዎች  ዋጋ በአለም አቀፍ ገበያ ላይ እንዲመሰረት አስችሎታል። 
መንግስት ወርሃዊ የነዳጅ ዋጋን መከለስከ ጀመረ በኋላ የህዝቡም ምሬት በዚያው ልክ አብሮ ከፍ ብሏል። በሀገሪቱ በየጊዜው የሚደረጉ የዋጋ ክለሳዎች የንግድ ስራዎችን  ብዙም የጠቀሙ አይመስሉም። የንግድ ስራ ባለቤቶች ቀጣይ ስራዎችን ለማቀድ ወይም በጀት ለማውጣት አስቸጋሪ ሆኖብናል ይላሉ። ምክንያታቸው ደግሞ የቀጣዩ ወር የነዳጅ ዋጋ ሳይከለስ በፊት በእጃቸው ላይ ያለ ክምችት መሸጥ አለበት። ይህ ከሆነ በኋላ የነዳጅ ዋጋው ተመልሶ ሊያሻቅብ ስለሚችል የንግድ ስራውን እንደሚያመሰቃቅለው ነው በምሬት የሚናገሩት ።
የምግብ ሸቀጣ ሸቀጥ መሸጫ መደብር ያላቸው ዳርሊንግተን ቺሌሼ ግን በዚህ ሃሳብ አይስማሙም ። 
"ዋጋ ሲጨምር "የቀደመ ክምችት ነው፣ እስኪያልቅ ድረስ እንጠብቃለን" አላሉም። እንደዚያ አይደለም። ወዲያው ነው ዋጋውን  የሚጨምሩት። ስለዚህ ሲቀንስ፤  ሁሉም ነገር ይቀንሳል ብለን እንጠብቃለን። የቀደመ ይሁን አዲስ ክምችት ዋጋ ሲቀንስ መቀነስ ይኖርበታል።  "
አሁንም በርካታ የንግድ ስራ ባለቤቶች እንደሚሉት በዛምቢያ በየወሩ የሚደረገው የነዳጅ ዋጋ ክለሳው ግራ አጋቢ እንደሆነባቸው ነው ። ይልቁኑ የነዳጅ ዋጋው በየወሩ ከሚከለስ በየስድት ወሩ ቢሆን የተረጋጋ ሁኔታ ሊፈጥርልን ይችላል ብለው ምክረ ሃሳብ ያቀርባሉ።
እንግዲህ አድማጮች በሁለት ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ያተኮረው የዕለቱ የትኩረት በአፍሪቃ ዝግጅታችንም የእስካሁኑ ነበር ። ጤና ይስጥልን።
ታምራት ዲንሳ 
አዜብ ታደሰ  

ታምራት ዲንሳ
አዜብ ታደሰ

Sambia Kazungula | Transport | Kazungula Brücke
ምስል Monirul Bhuiyan/AFP/Getty Images
Mosambik Hafen in Beira
ምስል Getty Images/AFP/G. Guercia
Baumaßnahmen Platz in Huambo Angola
ምስል Gianluigi Guercia/AFPGetty Images