1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ አብዮት ከ50 ዓመት በኋላ

ሐሙስ፣ ግንቦት 1 2016

ኢትዮጵያ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ እና የማኅበራዊ ስርዓቷን ከመሰረቱ የቀየረውን አብዮት ካስተናገደች ዘንድሮ ሃምሳ ዓመታት ገደማ አልፏል፡፡ በዚህም አገሪቱ ባለፈችበት ስርዓተ መንግስታት ቢያንስ ከ50 ዓመታት በፊት ከነበረው ስርዓተ መንግስት የተለየን መንገድ ብትከተልም ዛሬም ድረስ ግን በስርዓቶች ዴሞክራሲያዊነት ላይ የሚነሱ ጥያቄዎች በርካታ ናቸው፡፡

https://p.dw.com/p/4ffli
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት የተለያዩ ምሁራን የታደሙበት የጥናትና ውይይት መድረክምስል Seyoum Getu/DW

ከ50 ዓመት በኋላም የተፈለገው ለምን አልተሳካም?

ኢትዮጵያ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ እና የማኅበራዊ ስርዓቷን ከመሰረቱ የቀየረውን አብዮት ካስተናገደች ዘንድሮ ሃምሳ ዓመታት ገደማ አልፏል፡፡ በዚህም አገሪቱ ባለፈችበት ስርዓተ መንግስታት ቢያንስ ከ50 ዓመታት በፊት ከነበረው ስርዓተ መንግስት የተለየን መንገድ ብትከተልም ዛሬም ድረስ ግን በስርዓቶች ዴሞክራሲያዊነት ላይ የሚነሱ ጥያቄዎች በርካታ ናቸው፡፡ ዛሬ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ  የተለያዩ ምሁራን የታደሙበት የጥናትና ውይይት መድረክ አዘጋጅቶ ነበር ። በመድረኩ የኢትዮጵያ 50 ዓመታት ጎዞ እና ተግዳሮቱ ተገምግሞበታል፡፡

በዛሬው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መድረክ አመቻቺነት ከ50 ዓመት በፊት በነበረው የኢትዮጵያ ትልቁ አብዮት ዙሪያ በተካሄደው ውይይት የተለያዩ የፖለቲካ አመለካከት እና ተሳትፎ ያላቸው ምሁራን እና የተለያዩ ማህበረሰብ ተወካዮች ታድመዋል፡፡ የተለያዩ የፖለቲካ እይታ ያሏቸው ምሁራን እና ፖለቲከኞችም የጥናት ወረቀቶችን አቅርበው አወያይ ሃሳቦችን አንስተዋል፡፡

የ1960ዎቹ የተማሪዎች ንቅናቄ

ተወያዮቹ በሙሉ በኢትዮጵያ የተከሰተው የ1966ቱ አብዮት የኢትዮጵያን ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ሁናቴን በእጅጉ የለወጠ በሚለው ሃሳብ መደምደም ተስማምተው፤ አብዮቱን ተከትሎ የተከሰቱ እጅግ በርካታ ትሩፋቶች እና ተግዳሮቶች መኖራቸውንም አመላክተዋል፡፡

ለውይይቱ መነሻ ይሆንም ዘንድ የመጀመሪያውን የጥናት ወረቀት በተለይም ለአብዮቱ መነሳሻ ጥንስስ በሆነው የተማሪዎች ንቅናቄ ላይ በማተኮር ያቀረቡት የታሪክ ተመራማሪና ጸሃፊው ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ ናቸው፡፡

ፕሮፈሰር ባህሩ በኢትዮጵያ ባለፉት 50 ዓመታት ሁለት አብዮቶች በኢትዮጵያ መነሳታቸውን ጠቁመው አንደኛው በ1966 የደርግ መንግስትን ወደ ስልጣን ያመጣ ሲሆን ሌላኛው በ1983 የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ)ን ወደ ስልጣን ያመጣው አብዮት ናቸው ይላሉ፡፡ "አንደኛው አብዮት ከሁለተኛው የከፋ ሁን እንጂ ሁለቱም አብዮቶች የሰው ሕይወት በማጥፋት የታጀቡ ናቸው” ያሉት ፕሮፈሰር ባህሩ፤ በ1960ዎች ለተነሳው ሰፊው የተማሪዎች ንቅናቄ የመሬት ጭሰኝነት ፖሊሲ አለመቀየር እና በኋላም የመጣው የብሔር መብት ጥያቄ ጉልህውን ስፍራ እንደሚይዙ አመልክተዋል፡፡

ፕሮፈሰር ባህሩ በኢትዮጵያ ባለፉት 50 ዓመታት ሁለት አብዮቶች መነሳታቸውን ጠቁመዋል
ፕሮፈሰር ባህሩ በኢትዮጵያ ባለፉት 50 ዓመታት ሁለት አብዮቶች መነሳታቸውን ጠቁመዋልምስል Seyoum Getu/DW

ፕሮፈሰር ባህሩ በወቅቱ እጅግ የተማከለ ስልጣንን የያዙት ቀዳማዊ አጼ ኃይለስላሴ ከውስጥም ሆነ ከውጪ የሚመጣባቸውን የለውጥ ጥያቄዎች አዎንታዊ ምላሽ ሳይሰጡዋቸው መቅረታቸው "አብዮቱን ለመግታ ትልቅ አቅም እያላቸው” ለበርካቶች ደም መፋሰስ ምክኒያት የሆነውን አብዮትአይቀሬ አድርገውታል በሚልም ይተቹታል፡፡

የአብዮቱ አሉታዊ እና አዎንታዊ ገጽታዎች

በዛሬው የውይይት መድረክ የጥናት ጽሁፍ ያቀረቡት ሌላው ግለሰብ ከ1960ዎቹ ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (የሕወሓት የ41 ቀናት ስብሰባ ተጠናቀቀሕወሓት)ን ከመመስረት ጀምሮ አሁንም ድረስ በፖለቲካው እንቅስቃሴ ውስጥ ያሉ ዶ/ር አረጋዊ በርሔ ናቸው፡፡ ዶ/ር አረጋዊ በተለይም ለዶይቼ ቬለ በሰጡት አስተያየትም አብዮቱ ለዛሬ ያሸጋገረው ወረት እና አሉታዊ ተጽእኖው ጎን ለጎን የሚታዩ ናቸው ይላሉ፡፡ "በተለይም የነበረውን የመሬት ስሪት ከመሰረቱ በማፍረስ ለብዙሃኑ የሚበጅ የመሬት አስተዳደር እንዲዘረጋ አብዮቱ በጎ ሚና ነበረው፡፡ ይሁንና ከአያያዙ ጀምሮ ሂደቱ በነውጥ መመራቱ ዛሬም ድረስ የተሻገረን ግጭትና አለመረጋጋት እንድንወርስ አድርጎናል” በማለት አዎንታዊ እና አሉታዊ ገጹን አስቀምጠዋል፡፡

ጥናታዊ ጽሑፍ፦ የኢትዮጵያ አብዮት ከ50 ዓመት በኋላ
ጥናታዊ ጽሑፍ፦ የኢትዮጵያ አብዮት ከ50 ዓመት በኋላ ምስል Seyoum Getu/DW

የቋንቋ ፌዴራሊዝም አሉታዊ መልኮች

ከታዳሚዎቹም በተለይም በ1960ዎች እና ከዚያም በ1980ዎች አዲስ አቅጣጫን ባስያዙ የፖለቲካ ሁናቴዎች ሳቢያ አገሪቱ ከምን ጊዜም አስጊ ያሉት የቀውስ እና እልባት አልባ ግጭቶች ውስጥ መግባቷን ጠቁመው ሃሳብ አስተያየቶችን አንጸባርቀዋል፡፡ በተለይም የብሔር ፖለቲካ እና የቋንቋ ፌዴራሊዝሙ ከዚህ አንጻር ስላለው ጉልህ የሆነ አሉታዊ ተጽእኖ ተነስቶ መፍትሄው ተጠይቋል፡፡

ለዚህም ሃሳብ ምላሽ ከሰጡት አወያዮች ደግሞ የቀድሞ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) መስራች እና የአሁኑ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ዶ/ር ዲማ ነገዎ ይገኛሉ፡፡ "ኢትዮጵያ ትልቅ አገር እንደመሆኗ ሁሉንም አከባቢዎች ከአዲስ አበባ ማስተዳደር አዳጋች በመሆኑ ስልጣን ክፍፍል ማድረግ አግባብ ነበር” ያሉት ዶ/ር ዲማ ቅሬታዎች እና አሉታዊ ጉዳዮችን ለማረም መመከከርና ህገመንግስታዊ ማሻሻያም ካስፈለገ በውይይት ማድረጉ እንደሚበጅ በአስተያየታቸው አስረድተዋል፡፡  

ሥዩም ጌቱ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር